Call for participation

 In America, General

በሚኒሶታ ለምትኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልድ ኢትዮጵያውያን

በሚኒሶታ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ከተመሠረተ ረጅም ዓመታትን አስቆጥሯል። ይሁን እንጂ ላለፉት ዓመታት ማኅበረሰቡን ከመፍረስ ለመታደግ ከሚታትሩ ጥቂቶች በስተቀር እንደማህበር የጎላ እንቅስቃሴ ሲያደርግ አልታየም። ምንም እንኳ እንደኮሚኒቲ በስቴቱም ሆነ በፌደራል ደረጃ ሊኖረን ከሚገባው ተፅዕኖ አንፃር ተጠቃሽ ተግባር ማከናወን ባንችልም ከጥቂት ወራት በፊት በጣም ውስን በሆኑ አንዳንድ አባላት ከፍተኛ ጥረት የአነስተኛ ጽ/ቤት ህንፃ ባለቤት በመሆን እጅግ ቢያንስ ተሰባስበን መመካከር የምንችልበት ቋሚ አድራሻ ለማግኘት በቅተናል። ።

ይህ ግን አስፈላጊ የሆነው ጉዞአችን መጀመሪያ እንጂ መዳረሻ አይደለም። እንደማኅበረሰብ የተሻለ ሕንፃ ይገባናል። የሕንፃ ባለቤት መሆን ብቻ ሳይሆን የማህበረሰባችን አባላት በአሜሪካን ሀገር በጎ ተፅዕኖ ሲፈጥሩ ማየት እንሻለን። ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከሚያጋጥማቸው ልዩ ልዩ ችግሮች ወጥተው ውጤታማ እንዲሆኑ መደገፍ ይገባናል። በተለይም አልፎ አልፎም ቢሆን ያልተገባ ነገር ሊፈጽሙ በሚችሉ ሰዎች ምክንያት የሀገራችንም ስም በክፉ እንዳይነሳ እኛም በውጤቱ ተጎጂ እንዳንሆን ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። ለዚህም የማኅበረሰባችን አባላት በማወቅም ሆነ ባለማወቅ በሕገወጥ ድርጊቶች ተካፋዮች እንዳይሆኑ የማስተማር፣ የማሳወቅ እና የማረም ተግባራትን መፈፀም ይኖርብናል። ለማኅበረሰባችንም ሆነ ባጠቃላይ ለዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ ወይንም መሠረታችን ለሆነችው ኢትዮጵያም ሆነ ለመላው ዓለም የተለየ አስተዋጽኦ ለሚያበረክቱ ሰዎች እውቅና የመስጠት ልማድም ማዳበር እንዳለብን እንገነዘባለን። በተለይም ዓለም ዛሬ እየተጓዘችበት ያለውን መንገድ በማጤን መጪውን ጊዜ ሊመጥን የሚችል ተግባር ለማከናወን ከወዲሁ መዘጋጀት፣ ማቀድና እንቅስቃሴ መጀመር ግድ ይላል።

ከላይ የተጠቀሱትንና ሌሎች መሰል ተግባራትን በተሻለ ሁኔታ ለማከናወን የምንችለው ደግሞ ማኅበራችንን ስናጠናክር ነው። በሚኒሶታ የምንገኝ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ይህንን ማድረግ እንደምንችል ቀደም ሲል በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በተግባር አሳይተናል። ቤተ እምነቶቻችን በተለያየ መንገድ ከተዘፈቁበት ዕዳ እንዲወጡ፣ የየራሳቸው የማምለኪያ ቦታ እንዲኖራቸው እንዲሁም አገልጋዮቻቸው እንዳይቸገሩ በመደገፍ በርካታ ተግባራትን መከወን ችለናል። ይህንኑ ተግባራችንን ወደ አጠቃላይ የማኅበረሰቡ እንቅስቃሴ ብንለውጠው ምን ያህል ውጤታማ መሆን እንደምንችል መገመት ቀላል ነው። ባለራዕዮች ሆነን ማቀድ ከቻልን በሚኒሶታ ለማኅበረሰባችን አንድ የጋራ የሥራ፣ የንግድ እና የባህል ማዕከል ይኖረናል። ይህ ማዕከል ሥራ ፈላጊዎች የሥራ ዕድል የሚያገኙበት፣ አረጋውያን፦ የሚያርፉበት፣ እርስ በርስ የሚተዋወቁበት፣ ልምዶቻቸውን የሚያካፍሉበት፤ አዋቂዎች፦ የሚመካከሩበት፣ ሥራ የሚሰሩበት፣ ሥራዎቻቸውን የሚያስተዋውቁበት፣ ለራሳቸውም ዕረፍት የሚወስዱበት፤ ወጣቶች፦ የሕይወት ልምድ የሚቀስሙበት፣ ለሥራ የሚዘጋጁበት፣ የሚያጠኑበት፣ የሚዝናኑበት፣ ስለአገራቸው የሚማሩበትና ቅርርሳቸውን የሚያውቁበት፤ ሕፃናት፦ የሚማሩበት፣ ተጨማሪ ዕውቀት የሚገበዩበት፣ የሚጫወቱበት፣ የአገራቸውን ፊደል የሚመሩበት፣ አዕምሮአቸውን የሚያጎለብቱበት፤ በአጠቃላይ ኢትዮጵያውያን ባህላችንን የምንገልጽበት ማዕከል ይሆናል። መሠረታችን እንደተነሳበትም ሀገር እንደታሪካችንም ለሌሎች ምሳሌ የሚሆን ተግባር መከወን ይጠበቅብናል።  በአንድ ላይ ስንቆም ሁሉም ነገር በቀላሉ ሊሳካ እንደሚችል የገነባናቸው የእምነት ተቋማት ምስክሮች ናቸው።

ስለዚህ ይህንን ሁሉ ለማድረግ ከእኛ ምን ይጠበቃል? በግልስ ከእያንዳንዳቸን (ከእኔ) ምን ይጠበቃል? የሚለውን ጥያቄ አሁኑኑ መመለስ ይኖርብናል። የመጀመሪያው ርምጃ የማኅበሩ አባል መሆን ነው። አባል ከሆንን ደግሞ አነስተኛ የሆነውን ዓመታዊ መዋጮ ሳንዘገይ መክፈል ነው። በመቀጠልም ማኅበሩ በሚያድግበት ዙሪያ በሃሳብና በተግባር አስተዋጽኦ ለማበርከት መዘጋጀት ነው። ማኅበራችን አዲስ ወደገዛው ጽ/ቤት ብቅ በማለት ሀሳባችንን ማካፈል እና ማኅበሩን በመራጭነት፣ በተመራጭነት እንዲሁም በበጎ ፈቃደኝነት ማገልገል ነው።

ባሁኑ ወቅት ማኅበራችን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መገኘቱን ሁላችንም ልናውቅ ይገባናል። በመሆኑም ከዚህ ችግር ተባብረን እናወጣው ዘንድ ይህን ጥሪ ለማስተላለፍ ተገደናል። ጥሪው ማኅበሩን ሲመሩ የነበሩ የቦርድ አባላት የሥራ ጊዜያቸውን ጨርሰው ሊተኳቸው የሚችሉ አባላትን መምረጥ እና ከመካከላቸው ሊቀጥሉ የሚችሉ አባላትም እንዲቀጥሉ ለመወሰን የሚያስችል ነው። ማኅበራችን ከዚህ እጅግ አጣዳፊ ከሆነው ችግሩ ጋር ተያይዞ ከፊቱ የተደቀኑትን እጅግ ወሳኝ እና ጉልህ ጉዳዮች ለመከወን አዳጋች ሆኖበታል። የማኅበራችን ቦርድ ከአምስት ጊዜያት በላይ የስብሰባ ቀኖች ወስኖ ምርጫ ለማካሄድ ጥሪ ቢያደርግም ለመምረጥም ሆነ ለመመረጥ በቂ የሆነ የሰው ቁጥር ባለመገኘቱ ምርጫ ለማከናወን አልተቻለም። እንደሚታወቀው አሁን በሥራ ላይ የሚገኘው ቦርድ የአባላት ቁጥር በተለያየ ምክንያት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ ሄዷል። ያሉት አባላትም የሥራ ጊዜያቸው ስላለፈ የዕለት ተዕለት ሥራዎቻቸውን ማከናወን የሚያስችል ሕጋዊ መሠረት (mandate) እያጡ ነው። ለማኅበሩ መገልገያ የተገዛው ሕንፃ የሞርጌጅ ክፍያ ወቅቱን ጠብቆ በየጊዜው መፈፀም ይኖርበታል። ሕንፃውንም በአግባቡ ማስተዳደርና ደህንነቱን መጠበቅ ይጠይቃል። የዘንድሮው በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያውያን የእግር ኳስ ውድድር በሚኒሶታ አዘጋጅነት ይካሄዳል። ለዚህም ማኅበራችን በርካታ ሥራዎችን ማከናወን ይጠበቅበታል። እነዚህና ሌሎች ወሳኝ ተግባራት ከፊቱ የተደቀኑበት ማኅበራችንን ከገባበት አጣብቂኝ የማውጣት ተግባር በጎ የምናስብ ሰዎች ሁሉ ኃላፊነት ነው።

በመሆኑም ከላይ እንደተገልጸው የአባልነት ግዴታችንን በመፈጸም እ.አ.አ. ማርች 21 ቀን 2026 ከቀኑ 2፡00 pm ጀምሮ በሚካሄደው ስብሰባ ላይ ተገኝተን የቦርድ አባላት ምርጫ ላይ ተሳታፊ እንድንሆንና በቀጣይ ለሚከናወኑ ተግባራት በበጎ ፈቃደኝነት ለማገልገል ቃል እንድንገባ ከወዲሁ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን! የማኅበራችንን ህልውና በማስቀጠል የመጪው ጊዜ ታሪክ ኩራት አካል እንሆን ዘንድ ከእያንዳንዳችን የሚጠበቀውን ለማድረግ እንዘጋጅ!

ፈጣሪ ሁላችንንም ይባርከን!!!

ዲሴምበር 27 ቀን 2025

አስተባባሪ ኮሚቴው

Recent Posts
Contact Us

We're not around right now. But you can send us an email and we'll get back to you, asap.